Loading Bible Translation
First-time download in progress. This may take a few seconds…
Amharic Holy Bible Wordproject Bible
55 verses
1ያዕቆብም የላባ ልጆች ያሉትን ነገር። ያዕቆብ ለአባታችን የሆነውን ሁሉ ወሰደ፤ ይህንም ሁሉ ክብር ከአባታችን ከብት አገኘ ሲሉ ሰማ።
2፤ ያዕቆብም የላባን ፊት አየ፥ እነሆም ከእርሱ ጋር እንደ ዱሮው አልሆነም።
3፤ እግዚአብሔርም ያዕቆብን። ወደ አባትህ ምድር ወደ ዘመዶችህም ተመለስ፤ ከአንተም ጋር እሆናለሁ አለው።
4፤ ያዕቆብም ልኮ ራሔልንና ልያን ወደ በጎቹ ስፍራ ወደ ሜዳ ጠራቸው፥
5፤ እንዲህም አላቸው። የአባታችሁ ፊት ከእኔ ጋር እንደ ዱሮ እንዳልሆነ አያለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው።
6፤ እኔ ባለኝ ጕልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልሁ ታውቃላችሁ።
7፤ አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉ ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም።
8፤ ደመወዝህ ዝንጕርጕሮች ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕሮችን ወለዱ፤ ሽመልመሌ መሳዮቹ ደመወዝህ ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮችን ወለዱ።
9፤ እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ።
10፤ እንዲህም ሆነ፤ በጎቹ በጎመጁ ጊዜ ዓይኔን አንሥቼ በሕልም አየሁ፤ እነሆም፥ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ነበሩ።
11፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም። ያዕቆብ ሆይ አለኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁት።
12፤ እንዲህም አለኝ። ዓይንህን አቅንተህ እይ፤ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና።
13፤ ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ።
14፤ ራሔልና ልያም መልሰው እንዲህ አሉት። በአባታችን ቤት ለእኛ ድርሻና ርስት በውኑ ቀርቶልናልን?
15፤ እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቈጠርን አይደለንምን? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልና።
16፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሣው ይህ ሁሉ ሀብት ለእኛና ለልጆቻችን ነው፤ አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ።
17፤ ያዕቆብም ተነሣ፥ ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤
18፤ መንጎቹንም ሁሉ፥ የቤቱንም ዕቃ ሁሉ፥ በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ።
19፤ ላባ ግን በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፤ ራሔልም የአባትዋን ተራፊም ሰረቀች።
20፤ ያዕቆብም የሶርያውን ሰው ላባን ከድቶ ኮበለለ፥ መኮብለሉንም፥ አልነገረውም።
21፤ እርሱም ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ፤ ተነሥቶም ወንዙን ተሻገረ፥ ፊቱንም ወደ ገለዓድ ተራራ አቀና።
22፤ በ���ስተኛውም ቀን የያዕቆብ መኮብለል ለላባ ተነገረው።
23፤ ከወንድሞቹም ጋር ሆኖ የሰባት ቀን መንገድ ያህል ተከተለው፥ በገለዓድ ተራራም ላይ ደረሰበት።
24፤ እግዚአብሔርም ወደ ሶርያው ሰው ወደ ላባ በሌሊት ሕልም መጥቶ። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ አለው።
25፤ ላባም ደረሰበት፤ ያዕቆብም ድንኳኑን በተራራው ተክሎ ነበር፤ ላባም ከወንድሞቹ ጋር በገለዓድ ተራራ ድንኳኑን ተከለ።
26፤ ላባም ያዕቆብን አለው። ለምን እንዲህ አደረግህ? ከእኔ ከድተህ ኮበለልህ፥ ልጆቼንም በሰይፍ እንደ ተማረኩ ዓይነት ነዳሃቸው።
27፤ ስለምን በስውር ሸሸህ? ከእኔም ከድተህ ስለምን ኮበለልህ? በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርኸኝም?
28፤ ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቼን እንድስም ስለ ምን አልፈቀድህልኝም? ይህንም በስንፍና አደረግህ።
29፤ ክፉ አደርግባችሁ ዘንድ ኃይል ነበረኝ፤ ነገር ግን የአባታችሁ አምላክ ትናንት። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ ብሎ ነገረኝ።
30፤ አሁንም የአባትህን ቤት ከናፈቅህ ሂድ፤ ነገር ግን አምላኮቼን ለምን ሰረቅህ?
31፤ ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው። ልጆችህን ከእኔ የምትቀማኝ ስለመሰለኝና ስለፈራሁ ይህን አደረግሁ።
32፤ አምላኮችህን የምታገኝበት ሰው ግን እርሱ ይሙት፤ የአንተ የሆነውም በእኔ ዘንድ ይገኝ እንደ ሆነ በወንድሞቻችን ፊት ፈልግ፥ ለአንተም ውሰደው አለ። ራሔል እንደ ሰረቀቻቸው ያዕቆብ አያውቅም ነበርና።
33ላባም ወደ ያዕቆብ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን ወደ ሁለቱም ባሪያዎች ድንኳን ገባ፥ ነገር ግን አላገኘም። ከልያም ድንኳን ወጥቶ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ።
34ራሔልም ተራፊምን ወስዳ ከግመል ኮርቻ በታች ሸሸገች፥ በላዩም ተቀመጠችበት። ላባም ድንኳኑን ሁሉ ፈለገ፥ አንዳችም አላገኘም።
35እርስዋም አባትዋን። በፊትህ ለመቆም ስላልቻልሁ አትቆጣብኝ፤ በሴቶች የሚደርስ ግዳጅ ደርሶብኛልና አለችው። እርሱም ፈለገ፥ ነገር ግን ተራፊምን አላገኘም።
36ያዕቆብም ተቆጣ ላባንም ወቀሰው፤ ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው። የበደልሁህ በደል ምንድር ነው? ኃጢአቴስ ምንድር ነው ይህን ያህል ያሳደድኸኝ?
37አሁንም ዕቃዬን ሁሉ በረበርህ፤ ከቤትህስ ዕቃ ሁሉ ምን አገኘህ? እነርሱ በእኛ በሁለታችን መካከል ይፈርዱ ዘንድ በወንድሞቼና በወንድሞችህ ፊት አቅርበው።
38ሀያ ዓመት ሙሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ በጎችህና ፍየሎችህ አልጨነገፉም፤ የመንጎችህንም ጠቦቶች አልበላሁም፤ አውሬ የሰበረውን አላመጣሁልህም ነበር፤
39እኔ ስለ እርሱ እከፍልህ ነበርሁ፤ በቀንም በሌሊትም የተሰረቀውን ከእጄ ትሻው ነበርህ።
40የቀን ሐሩር የሌሊት ቍር ይበላኝ ነበር፥ እንቅልፍም ከዓይኔ ጠፋ።
41እንዲሁ በአንተ ቤት ሀያ ዓመት ነበርሁ አሥራ አራት ዓመት ስለ ሁለቱ ሴቶች ልጆችህ፥ ስድስት ዓመትም ስለ በጎችህ ተገዛሁልህ፤ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለዋወጥኸው።
42የአባቴ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም ፍርሃት ከእኔ ጋር ባይሆንስ ዛሬ ባዶ እጄን በሰደድኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር መከራዬንና የእጆቼን ድካም አየ፥ ትናንትም ገሠጸህ።
43ላባም እንዲህ ብሎ ለያቆብ መለሰለት። ሴቶቹ ልጆች ልጆቼ ናቸው፥ ሕፃናቱም ሕፃናቴ ናቸው፥ መንጎቹም መንጎቼ ናቸው፥ የምታየውም ሁሉ የእኔ ነው፤ ዛሬም በእነዚህ በሴቶች ልጆቼና በወለዱአቸው ልጆቻቸው ላይ ምን ላደርግ ይቻላል?
44አሁንም ና፥ አንተና እኔ ቃል ኪዳን እንጋባ፤ በእኔና በአንተ መካከልም ምስክር ይሁን።
45ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አቆመ።
46ያዕቆብም ወንድሞቹን። ድንጋይ ሰብስቡ አላቸው፤ እነርሱም ድንጋይ ሰብስበው ከመሩ፤ በድንጋዩም ክምር ላይ በሉ።
47ላባም ይጋር ሠሀዱታ ብሎ ጠራት፤ ያዕቆብም ገለዓድ አላት።
48ላባም። ይህች ክምር በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ናት አለ። ስለዚህም ስምዋ ገለዓድ ተባለ፤
49ደግሞም ምጽጳ ተባለ። እኛ በተለያየን ጊዜ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ሆኖ ይጠብቅ ብሎአልና።
50ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም በላያቸው ሚስቶችን ብታገባባቸው ከእኛ ጋር ያለ ሰው የለም፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ምስክር ነው።
51ላባም ያዕቆብን አለው። በእኔና በአንተ መካከል እነሆ ይህች ክምር፥ እነሆም ያቆምኋት ሐውልት፤
52እኔ ወደ አንተ ይህችን ክምር እንዳላልፍ፥ አንተም ለክፋት ወደ እኔ ይህችን ክምርና ይህችን ሐውልት እንዳታልፋት፥ ይህች ክምር ምስክር ናት፥ ይህችም ሐውልት ምስክር ናት።
53የአብርሃም አምላክ የናኮርም አምላክ የአባታቸውም አምላክ በእኛ መካከል ይፍረድ። ያዕቆብም በአባቱ በይስሐቅ ፍርሃት ማለ።
54ያዕቆብም በተራራው ላይ መሥዋዕትን ሠዋ፥ ወንድሞቹንም እንጀራ እንዲበሉ ጠራ፤ እነርሱም እንጀራን በሉ፥ በዚያም በተራራ አደሩ።
55ላባም ማልዶ ተነሥቶ ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቹን ሳመ ባረካቸውም፤ ላባም ተመልሶ ወደ ስፍራው ሄደ።