Loading Bible Translation
First-time download in progress. This may take a few seconds…
Amharic Holy Bible Wordproject Bible
18 verses
1በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን ወደ ሕዝቅያስ ልጅ ወደ አማርያ ልጅ ወደ ጎዶልያስ ልጅ ወደ ኵሲ ልጅ ወደ ሶፎንያስ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2፤ ነገርን ሁሉ ከምድር ፊት ፈጽሜ አጠፋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
3፤ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ የሰማይን ወፎችና የባሕርን ዓሣዎች ማሰናከያንም ከኃጢአተኞች ጋር አጠፋለሁ፤ ሰውንም ከምድር ፊት እቈርጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
4፤ እጄንም በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እዘረጋለሁ፤ ከዚህም ስፍራ የበኣልን ቅሬታና የጣዖታቱን ካህናት ስም አጠፋለሁ፤
5፤ በሰገነትም ላይ ለሰማይ ሠራዊት የሚሰግዱትን፥ በእግዚአብሔርና በንጉሣቸው በሚልኮም ምለው የሚሰግዱትን፥
6፤ እግዚአብሔርንም ከመከተል የተመለሱትን፥ እግዚአብሔርንም ያልፈለጉትንና ያልጠየቁትን አጠፋለሁ።
7፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፥ እግዚአብሔር መሥዋዕትን አዘጋጅቶአልና፥ የጠራቸውንም ቀድሶአልና በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ።
8፤ በእግዚአብሔርም መሥዋዕት ቀን አለቆችንና የንጉሥን ልጆች እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እቀጣለሁ።
9፤ በዚያም ቀን በመድረኩ ላይ የሚዘልሉትን፥ የጌታቸውን ቤት ዓመፃንና ሽንገላን የሚሞሉትን እቀጣለሁ።
10፤ በዚያ ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ከዓሣው በር የጩኸት ድምፅ፥ ከከተማውም በሁለተኛው ክፍል ውካታ፥ ከኮረብቶቹም ታላቅ ሽብር ይሆናል።
11፤ እናንተ በመክቴሽ የምኖሩ ሆይ፥ የከነዓን ሕዝብ ሁሉ ጠፍተዋልና፥ ብርም የተሸከሙ ሁሉ ተቈርጠዋልና አልቅሱ።
12፤ በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን በመብራት እመረምራለሁ፤ በአተላቸውም ላይ የሚቀመጡትን፥ በልባቸውም። እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፥ ክፉም አያደርግም የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ።
13፤ ብልጥግናቸውም ለምርኮ ይሆናል፥ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፤ ቤቶችንም ይሠራሉ፥ ነገር ግን አይቀመጡባቸውም፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁን ግን አይጠጡም።
14፤ ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል፤ ኃያሉም በዚያ በመራራ ልቅሶ ይጮኻል።
15፤ ያ ቀን የመዓት ቀን የመከራና የጭንቀት ቀን፥ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፥ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፥
16፤ በተመሸጉ ከተሞችና በረዘሙ ግንቦች ላይ የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን ነው።
17፤ በእግዚአብሔርም ላይ ኃጢአት ሠርተዋልና እንደ ዕውር እስኪሄዱ ድረስ ሰዎችን አስጨንቃለሁ፤ ደማቸውም እንደ ትቢያ፥ ሥጋቸውም እንደ ጕድፍ ይፈስሳል።
18፤ በእግዚአብሔርም ቍጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ እርሱም በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥኖ ይጨርሳቸዋልና ምድር ሁሉ በቅንዓቱ እሳት ትበላለች።